ኮሌጁ 886 ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመረቋል ።
ሉሲ ኮሌጅ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከ 20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ያፈራ ሲሆን ኮሌጁ በዛሬው እለትም በኢትዮ-ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፣ ተመራቂ ተማሪዎችና ፣ የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ተማሪዎቹን በታላቅ ድምቀት አስመርቋል ።
በዚሁም የምረቃት ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሀርቢ ቡህ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራችን ኢትዮጲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ለመመረቅ በመብቃታቸው ከፍተኛ የሆነ ሀላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን ተናግረው ተመራቂ ተማሪዎችም በተለይም በከተማዋ ላይ የሚካሄዱ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ላይ የራሳቸውን ጉልህ አሻራ ሊያስቀምጡ እንደሚገባ አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረዋል ።
ሉሲ ኮሌጅ በዲግሪ መርሀ-ግብር 222 የሚሆኑ ወንዶች ፣ 300 ሴቶች በአጠቃላይ 522 ተማሪዎች እንዲሁም በቴክኒክና ሞያ ዘርፍ ደግሞ በደረጃ 4 :- 161 የሚሆኑ ወንዶች ፣ 203 ደግሞ ሴቶች በድምሩ 364 ተማሪዎች ” በአጠቃላይ ኮሌጁ 886 ተማሪዎችን ” በዛሬው እለት ማስመረቅ መቻሉን የሉሲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ\ሮ መቅደስ መሀሪ ተናግረው ተቋሙ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችንና ጠቃሚ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን እያሳተመ እንደሚገኝም ወ\ሮ መቅደስ ተናግረዋል ።
በእለቱ ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎች በበኩላቸው በነበራቸው የትምህርት ቆይታ ፈታኝ የሚባሉ ወቅቶችን አልፈው ለምርቃት መብቃታቸውን ተናግረው በቀጣይም በሚሰማሩበት የስራ መስክ በታማኝነትና በቅንነት ነዋሪው ህብረተሰብን ለማገልገል መዘጋጀታቸውንም ተመራቂ ተማሪዎቹ በእለቱ ተናግረዋል ።


