የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፤ ከፍተኛ አመራሮችና የሃይማት አባቶች በተገኙበት በከንቲባ ፅ/ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ከድር ጁሃር በአስተዳደራችን ባሉት 10 የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ መከላከያ የክትባት ዘመቻ ቀናት ከ60 ሺ በላይ ሰዎችን ለመከተብ ዕቅድ መያዙንና ዝግጅቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረው ህብረተሰቡ በየአካባቢው ባሉ የጤና ተቋማትና የዘመቻው ሥራ ተደራሽ በሚሆንባቸው ስፍራዎች በመገኘት ክትባቱን እንዲከተብ አሳስበዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች፤ የግልና የመንግስት ተቋማት እና በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት ከአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገርና ፕሮግራም በማስያዝ ባሉበት የሥራ ቦታዎች ክትባቱን መውሰድ እንደሚችሉ ጠቁመው ለኮቪድ -19 ወረርሽኝ መከላከያ የተዘጋጁ የክትባት ዓይነቶችን በተመለከተ በተሳሳቱ መረጃዎች ሳይዘናጋ በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እየወሰዱት ያለውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶችን በመከተብ ወረርሽኙ እያስከተለ ካለው ከፍተኛ ህመምና ሞት ራሱን ሊታደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶችን በተመለከተ ከተሳሳተና ካልተጣራ መረጃ ማህበረሰቡ ራሱን መጠበቅ እንደሚገባውና የትኛውም ሃይማኖት ቢሆን ክትባቱን መከተብን የማይከለክል በመሆኑና እኛም የየሃይማኖቱ መሪዎች ለምዕመኖቻችን አርዓያ ለመሆንና ራሳችንንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከሚያስከትለው ከፍተኛ ህመምና ሞት ለመጠበቅ ክትባቱን መውሰዳችንን በየሃይማኖት ተቋማቶች ያሉ ምዕመናን ይህንኑ ሊረዱ ይገባል ብለዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ ጨምረውም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶች ዙሪያ የተሳሳተ መረጃ የሚያስተላልፉ አካላት ፈጣሪ ከማይወደው ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ በማስተላለፍ ምዕመናን በ10ሩ የዘመቻ ቀናት የኛን የሃይማኖት አባቶቻውን አርዓያነት በመከተል ክትባቱን እንዲወስዱ ጥሪቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የክትባት ዘመቻው ከህዳር 6-15 /2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ቀደም ብለው በሰጡት መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፦ድሬዳዋ ጤና ቢሮ


