በ 06 ቀበሌ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉትን የፍሳሽ ቆሻሻዎች የማስወገድ ስራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ ።

    ከተማችን ድሬዳዋን ፅዱና ውብ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ትሆን ዘንድ በየሳምንቱ ቅዳሜ ጠዋት ከፍተኛ የከተማዋን አመራሮች አሳታፊ ያደረገ የፅዳት ዘመቻ በመካሄድ ላይ ይገኛል ። ይኸውም በአመራሩ የተጀመረው የፅዳት ዘመቻ ነዋሪው ህብረተሰብ በባለቤትነት ወስዶ ይሰራ ዘንድም የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ ።
    ከዚሁ የፅዳት ዘመቻ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት በ 06 ቀበሌ ከፍተኛ የሆነ የፍሳሽ ቆሻሻ እንደነበርና ይህንንም ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድም የቀበሌ አመራር ፣ የአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ፣ ደንብ ማስከበር እንዲሁም ውሀና ፍሳሽ በጋራ በመሆን በአካባቢው ላይ የሚስተዋለውን የፍሳሽ ቆሻሻን ለመቅረፍ በተደረገው ስራ አመርቂ የሆኑ ስራዎች መሰራት መቻላቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ-አስኪያጅ ፅህፈት ቤት ምክትል ቢሮ ሀላፊና የደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ፋህሚ ሙሜ ተናግረው ከዚሁ ስራ ጋር ተያይዞ ከመጠን በላይ ፍሳሾችን በመልቀቅ ያስቸገሩ 60 የሚሆኑ አካላት ላይ የቅጣት እርምጃ እንደተወሰደና በቀጣይም አሁን ላይ የፍሳሽ ቆሻሻዎችን የማስወገዱ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ ፋህሚ ሙሜ የተናገሩት ።
    የፍሳሽ ቆሻሻው በተለይም ከቀፊራ አንስቶ እስከ ቀብሪ ጆሌ ባሉ አካባቢዎች ላይ ይስተዋል እንደነበርና ይህንንም ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድም በአካባቢው ላይ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስጠት እንዲሁም ከደንብ አስከባሪዎች ጋር በጋራ በመቀናጀትና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን የ 06 ቀበሌ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዚያድ መሀመድ ተናግረዋል ።
    ከዚህ ቀደም በአካባቢው ላይ የነበረው የፍሳሽ ቆሻሻ ለስራም ሆነ ለኑሮ በእጅጉ አስቸጋሪ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረው አሁን ላይ ግን በተሰራው ስራ አበረታች የሆነ ለውጥ መምጣቱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።