የሀገርን ጥሪ የተቀበሉ ከ200 በላይ የቀድሞ ሰራዊትና ምልስ ሰራዊት አባላት በድሬዳዋ አስተዳደር ሽኝት ተደረገላቸው።
የሽብርተኛውን ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራና የከፈተውን ጦርነት ለማክሸፍ የሚካሄደውን ሀገር የማዳን ጥሪን በመቀበል የቀድሞ ጦር ሰራዊትና የመከላከያ ሰራዊት ምልስ አባላት ዛሬ ሽኝት ተደርጎላቸዋል።
በስነስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት ዘማቾች ወንጀለኛው ቡድን ሀገሪቱ ላይ የጀመረውን የንጹሀን ዜጎች እልቂትና ሀገርን የማፍረስ እኩይ ሴራን ለማምከን በሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ጥረት የሀገርን ጥሪ ምላሽ በመስጠታቸው የሚያኮራ ተግባር እንደመሆኑ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዘመቻው ሀገርን በማስቀደም ጦርነቱን በድል ለመደምደም የሚጠበቅባቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪ እስተላልፈዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የድሬዳዋና የሀረር ላይዘን ሀላፊ ኮሎኔል ዮናስ ሮባ በበኩላቸው እንደገለጹት የሽብርተኛው ቡድንም የጥፋት ሴራን ለማክሸፍ የሀገርን ጥሪ በመቀበል የሰራዊቱን የተቀላቀሉ የቀድሞ ጦር ሰራዊትና የመከላከያ ሰራዊት ምልስ አባላት በጥቅሉ 202 ያህል መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ዘማቾቹ በወቅቱ እንደገለጹት ቀደም ሲል በሰራዊቱ ውስጥ በነበሩባቸው አመታት የጁንታው ቡድን አባላት የሆኑ አዛዦች በሚፈጽሙባቸው ሴራና ደባ ከሰራዊቱ እንዲገለሉ እንዳስገደዷቸው ጠቅሰው በጓዶቻቸው ላይ ጥቅምት 24 ፣ 2013 ዓ.ም የፈጸሙት አስነዋሪ ወንጀልና አሁንም ሀገርን ለማፍረስ እያካሄዱ የሚገኘውን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ ተናግረዋል።
በሽኝት ስነስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የመከላከያ ሰራዊት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ምንጭ፦DireMassMedia
ፎቶ፦ከንቲባ ጽ/ቤት


