16 ተኛው የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአል በድሬዳዋ አስተዳደር አዘጋጅነት የፊታችን ህዳር 29 የሚከበር ሲሆን በአስተባባሪነት ደግሞ የኢትዮጲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ። ለዚሁም በአል ይሆን ዘንድም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር በሚከበረው በአል ላይም ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም ፣ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ለቀጣዩ ክልል ማስረከብ ፣ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ ፕሮግራም እንዲሁም ለበአሉ ወደ ከተማችን የሚመጡ እንግዶችን በክብር የመቀበል ፕሮግራም የሚካሄድ ይሆናል ።
ከዚሁ 16 ኛው የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአል ጋር ተያይዞ ለበአሉ እየተደረጉ ያሉትን ቅድመ ዝግጅቶች በድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ የሚመራ ቡድንና አስተባባሪ ኮሚቴ ጉብኝት አድርገዋል ። በተለይም ለበአሉ ከ 11 ክልሎችና ከአዲስ አበባ መስተዳደር ከ 700 በላይ የሚሆኑ እንግዶች ወደ ከተማዋ እንደሚመጡና ለዚሁም በአል እየተደረጉ ያሉት ስራዎች ከ 90 ፐርሰንት በላይ መጠናቀቁን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረው ቀሪ ስራዎችም በቀጣይ ቀናት የሚጠናቀቅ መሆኑንም ተናግረዋል ።
አቶ ሀርቢ ቡህ አክለውም 16 ኛው የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአል በተሳካ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድም የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል ።


