ከአዲስ የመንግስት ምስረታ ጋር ተያይዞ በከተማችን ድሬዳዋ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች ፣ በድሬዳዋ አስተዳደር ከሚከበረው 16 ተኛው የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል ጋር ተያይዞ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ከሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞም በድሬዳዋ አስተዳደር ያሉ እንቅስቃሴዎችና መንግስት እያከናወናቸው ያሉትን ስራዎች አስመልክቶ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሀገር ደረጃ ከተመሰረተው አዲስ የመንግስት ምስረታ ጋር ተያይዞ በድሬዳዋ አስተዳደርም አዲስ የመንግስት ምስረታ የተካሄደ ሲሆን በአዲስ ምእራፍ ወደ አዲስ ተግባር ለመግባት ይቻል ዘንድም በከተማዋ ላይ ለመስራት የታቀዱትን ስራዎች ለነዋሪው ህብረተሰብ ቃል የተገባ ስለሆነም ይህም የተገባውን ቃል ተግባራዊ የማድረግ ስራዎች በማግስቱ እንደተጀመሩና እነዚህ ስራዎች በተለይም የከተማዋን ስምና ዝና የመመለስ ፅዱና ውብ ብሎም ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ትሆን ዘንድም መላው የከተማዋ አመራሮች በቁርጠኝነት በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የፅዳት ዘመቻ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙም አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።
አቶ እስቂያስ አክለውም በድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የአእምሮ ህሙማን የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሰባሰብና ከሚሽን ኦፍ ቻሪቲ ጋር በጋራ በመሆን ወደ ማእከል እንዲገቡና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የማድረጉ ስራዎች እንደሚሰሩና ከአረጋዊያን ጋር ተያይዞ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውና በአካባቢያችን ላይ የሚገኙ አረጋዊያን በማሰባሰብና ወደ ማእከል በማስገባት ድጋፍና ክትትል እንደረግላቸው ገልፀዋል ። ከጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ አካላት ጋር ተያይዞ ቤተሰቦቻቸው በከተማው ላይ የሚገኙ አካላት ከቀበሌ ጋር በመነጋገር ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ እንደሚደረግና ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ወደ ከተማችን የመጡትን ደግሞ ከመጡበት ክልሎች ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ነገር በማዘጋጀት ወደ መጡበት ኡካባቢ የመመለስ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነና ሌላው ከተማን የማስዋብ የማስተካከልና ውብና ፅዱ ከማድረግ አኳያ በከተማዋ የሚገኙ ተንቀሳቃሽ ሱቆች ህጋዊ የሆኑት ከዋናው መንገድ ውጪ ተለዋጭ ቦታ እንደሚዘጋጅላቸውና ህጋዊ ያልሆኑ ሱቆች ደግሞ በህጉ መሰረት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድና ይህም ስራ በሁሉም ቀበሌዎች እንደሚሰሩም አቶ እስቂያስ ተናግረዋል ።
ከሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞም በድሬዳዋ አስተዳደር ያሉ እንቅስቃሴዎችና መንግስት እያከናወናቸው ያሉትን ስራዎች አስመልክቶ አካባቢህን ጠብቅ ወደ ግንባር ዝመት መከላከያን ደግፍ በሚለው መርህ መሰረት የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝና ከነዚህም ስራዎች ውስጥ ከአካባቢ ጥበቃ አኳያ ህብረተሰቡን ባሳተፈና ከወትሮ በተለየ መልኩ የፀጥታ አካላት በቂ ዝግጅት በማድረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ከፍተኛውንም ድርሻ በመውሰድና ሌሎች የፀጥታ አካላትንም በማሳተፍና በአካባቢው ያሉትን የፀጥታ አካላት በቅንጅት በማሳተፍ 16 ተኛው የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል ከወትሮው በተለየ መልኩ እንዲከበርና የሀገርን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ ሁኔታ በቂ የሆነ ዝግጅት መሰራቱን የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።
አጠቃላይ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀብት ማሰባሰብ ስራዎችን ከመስራትና ድጋፎችን ከማድረግ አኳያ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝና በቀጣይም በአፋር እንዲሁም በአማራ ክልል አካባቢዎች አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግና ከዚህ ባለፈም ደግሞ ነዋሪው እራሱን የዘመቻው አንድ አካል በማድረግና ከመዝመት ባለፈ በተለያዩ ግንባሮች ለሚደረጉ ዘመቻዎችም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚገባም አቶ እስቂያስ ተናግረዋል ።
የፊታችን ህዳር 29 በድሬዳዋ አስተዳደር ከሚከበረው 16 ተኛው የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል ጋር ተያይዞ ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶችና ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣቹ ፕሮግራም ብሎም ለበአሉ 500 የሚሆኑ የክልልና የፌደራል ተወካዮች እንዲሁም ደግሞ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ 100 የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጠቃላይ ከ 600 በላይ አካላት አሳታፊ ያደረገ ሲምፖዚየም የሚካሄድ ሲሆን ከዚህ ባለፈም የንግድ ትርኢትና ባዛር ፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ጎን መሆናችንንም ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድም የበአሉ ተሳታፊና ታዳሚያንን አሳታፊ ያደረገ የደም ልገሳ ፕሮግራም እንደሚካሄድም አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።
ለበአሉም ከፍተኛ የሆነ ትኩረት በመስጠትና ኮሚቴ በማዋቀርም ዘርፈ-ብዙ ስራዎች እንደተሰሩና ነዋሪው ህብረተሰብም ለበአሉ ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ከመቀበል አንስቶ በአሉ በሰላም ይካሄድ ዘንድም የራሳቸውን አስተዋፆ መወጣት እንደሚገባም ነው አቶ እስቂያስ የተናገሩት ።
አሁን ላይ የተጀመሩና ከተማዋን ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና ላይ ለማምጣት የሚሰሩ ስራዎች በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ እስቂያስ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት ።


