በሶማሌ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰቱ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁለቱ ክልሎች ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ገዳማይቱ ፣ እንዱፎ እና ገርበኢሴ በተባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ይከሰቱ ነበሩ ግጭቶች ሞት እና መፈናቀል ከማስከተል ባለፈ ሁለቱን ክልሎች የቃል እሰጣ አገባ ውስጥ ሲያስገባቸው ቆይቷል። የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ጅግጅጋ ተገኝተው ከሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ማጠቃለያም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል የተባለ ስምምነት ላይ ተደርሷል።


