ዘንድሮ በድሬዳዋ ለሚኪያሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው::

    በድሬዳዋ አስተዳደር ዘንድሮ ለ4ተኛ ጊዜ ለሚኪያሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አበረታች የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ የደን ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።
    በዋና ዳይሬክተሩ አቶ ከበደ ይማም የተመራ ቡድን ዛሬ ረፋድ ድሬዳዋ ተገኝቶ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባውን ዘመናዊ የችግኝ ማፍያ ጣቢያና ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ እየተካሄዱ የሚገኙትን እንቅስቃሴዎች ጎብኝቷል፡፡
    በፌደራል መንግስት ድጋፍ በመላው አገሪቱ ከተገነቡት ዘመናዊ የችግኝ ጣቢያዎች የድሬዳዋና የጅግጅጋ በአርአያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ከበደ በጉብኝቱ ላይ ገልጸዋል ፡፡
    በዚህ ችግኝ ጣቢያና በሌሎቹ እየተካሄዱ የሚገኙ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ማፍላት ሂደት የሚበረታታ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል፡፡
    ድሬዳዋ የሚፈሉት አገር በቀል ችግኞች የአየር ንብረትን በመለወጥና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሂደትን እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
    ይበልጥኑ ድሬዳዋ የሚዘጋጁ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ ከጅቡቲ መንግስት ጋር ያለንን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚያጠናከሩ ናቸው ብለዋል፤ለአስተዳደሩ አስፈላጊው ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
    የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው ዘንድሮ ለ4ተኛ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የደንና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡
    ከሁለት ሚሊዮን ውስጥ 150 ሺዎቹ ለጅቡቲ የሚላክና 50 ሺዎቹ ደግሞ ለምስራቅ ተጎራባች ክልሎች በማሰራጨት ምስራቁን በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር በተቀናጀ መንገድ ይሰራል ብለዋል፡፡
    አገር በቀል የጥላና የፍራፍሬ ችግኞቹ በገጠርና በከተማ በሚገኙ 26 ችግኝ ጣቢያዎች በድሬዳዋ ግብርና ቢሮና በባለስልጣኑ ቅንጅት እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዱ ናቸው፡፡
    እስከ አሁን 1.2 ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ ሲሆን የቀሩትም በሚፈለገው ጊዜ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
    ባለፉት ሶስት ዓመታት በድሬዳዋ ከተተከሉት 4.3 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ በአማካይ 62 በመቶ መጽደቃቸውን ገልጸው ህብረተሰቡ ለሚተክላቸው ችግኞች ምንግዜም በባለቤትነት መንከባከብ አለበት ብለዋል፡፡
    የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢሊያስ አሊይ በበኩላቸው ችግኝ መትከልና ተንከባክቦ ማሳደግ ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ባለቤት የሌለው ችግኝ እንዳይተከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡
    እሳቸው እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ ለመጠበቅና የገጠሩን ህብረተሰብ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን እያገዙ በመሆኑ አጠናክሮ ለመቀጠል እየተሰራ ይገኛል ፡፡
    ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በመላው አገሪቱ በሚካሄደው 4ተኛው የአረንጓዴ አሻራ ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
    በድሬዳዋ ዘንድሮ ለጅቡቲ የሚላውን ጨምሮ ሁለት ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ተመልክቷል፡፡