በድሬዳዋ አስተዳደር በሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ላይ ከጠዋት 12 ሰአት እስከ 4 ሰአት ድረስ በከተማዋ ላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዝግ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል ። በዚሁም ጉዳይ ዙሪያ ለመምክር በዛሬው እለት በራስ-ሆቴል መሰብሰብያ አዳራሽ ከሀይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል ።
በተለይም እድሜያቸው የገፍ እናት አባቶች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እሁድ ወደ ቤተ-እምነቶች ለመሄድ የትራንስፖርት አገልግሎት ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ በእጅጉ እየተቸገሩ ከመሆናቸውም ባለፈ የጤና እክል ያለባቸው አካላትም ረጅም እርቀት በእግር ለመሄድ መቸገራቸውንም የሀይማኖት አባቶቹ በውይይቱ ላይ አንስተዋል ።
እሁድ የእረፍት ቀን ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ተለያዩ ቤተ-እምነቶች እንደሚሄዱና ቤተ-እምነቶቹም ከነዋሪዎቹ መኖሪያ ቤት መራቅ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ መስተጓጎሎችን እንደፈጠባቸውና እሁድ ጠዋት ለትራንስፖርት ዝግ እንዲሆን የተወሰነው ውሳኔ ሊነሳ ወይም ሊስተካከል እንደሚገባም ነው የሀይማኖት አባቶቹ የጠየቁት ።
በድሬዳዋ አስተዳደር አንዱን እምነት ከአንዱ እምነት ጋር ለማጋጨት የሚጥሩ አካላት እንዳሉና ነገር ግን በከተማዋ ላይ የተለያዩ እምነቶች በጋራ ተቻችለውና ተከባብረው ለዘመናት የኖሩባት ከተማ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ እምነቶችን ለማጋጨት የሚጥሩ አካላት በፍፁም እንደማይሳካላቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
ክቡር ከንቲባው አክለውም እሁድ ጠዋት በከተማዋ ላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዝግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከነዋሪው ህብረተሰብ እንዲሁም ከሀይማኖት አባቶች የተነሱትን ጥያቄዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እሁድ ጠዋት ሙሉ ከተማው ለትራንስፖርት ክፍት እንዲሆን ነገር ግን ከኮኔል ድልድይ አንስቶ ከዚራ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ለትራንስፖርት ዝግ እንደሚሆንም ክቡር ከንቲባው በውይይቱ ላይ ተናግረዋል ።
የከተማው ነዋሪዎች እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እራሳቸውን ከተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲከላከሉ ለማድረግ እንዲሁም የነዳጅን ብክነትን ለመቀነስ በማለም የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እሁድ ለተወሰኑ ሰአቶች እንደተገደበ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ገልጸዉ ነገር ግን እሁድ ለትራንስፖት ዝግ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ የሀይማኖት አባቶች ያነሷቸው ጥያቄዎች ትክክል እንደሆኑና በቀጣይም ለከተማዋ እድገትና ብልፅግና በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በእለቱ ተናግረዋል ።


