የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ሲቻል መሆኑ ተገለጸ

    እንደ አገር ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ሲቻል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሮች አስታወቁ።
    በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተሰናዳውና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያተኮረው የድሬደዋው የፓናል ውይይት ተጠናቋል።
    በመድረኩ በነበረው ውይይት ላይ ለተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የእለቱ ጽሁፍ አቅራቢዎች የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኃላፊ አቶ ጀማል አህመድ ምላሽ ሰጥተዋል።
    መድረኩን ያጠቃለሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ ከባለሀብቶች የተናሳው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ሲቻል ነው ብለዋል።
    መንግስት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ቅድሚያ ማግኘት ያለባቸውን ዘርፎች ለይቶ እየሰራ መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ግን ያመነጩትን የወጭ ምንዛሬ መጠቀም መብታቸው ነው በሚል ፈቅዶ ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል።
    አምራች ኢንዱስትሪው በሀገር በቀል ኢኮኖሚው ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ ዘርፍ የአገሪቷ የእድገት ሞተር በመሆኑ መንግስት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
    ዘርፉ የሚያድገው በዋናነት በግል ባለሀብቱ ተሳትፎ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በመንግስት በኩልም መሠረተ ልማትን ማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቢሮክራሲ ማቅለል ስለሚጠበቅ በዚያ አግባብ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ አብራርተዋል።
    የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብት ለኢኮኖሚው ያስፈልጋሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ የመንግስት ዋና አላማ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን መደገፍና ማብቃት ነው በዚህም ብዙውን ጊዜ በውጭ ባለሀብቶች ወቀሳ ሳይቀር እንደሚቀርብበት ገልጸዋል።
    የመንግስት ፍላጎቱም አላማውም የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ዘርፉ በበላይነት በእነሱ እንዲመራ ነው፤ ነገር ግን ኢንዱስትሪው በአገር ውስጥ ብቻ የሚሳካ አይደለም፤ ምክንያቱም የፋይናንሥ የቴክኖሎጂና መሰል አቅማችን ገና ውስን በመሆኑ ያስፈልጉናል፤ ሁለቱም ተቀናጅተው እንዲሰሩ መደገፍ የመንግስት ተልዕኮና ሥራ ነው፤ ሁለቱንም እየደገፍን እንቀጥላለን ሲሉም ነው አቶ አህመድ ያብራሩት።
    በተመሳሳይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግርን ለመፍታት የመጀመሪያውና መሠረታዊው መፍትሄ ምርትን ማሳደግ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል።
    የሌሎች አገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ይሄንኑ በመሆኑ ምርት ላይ ርብርብ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
    በእኛ ዘንድ ያለው ችግር የፓሊሲ ሳይሆን ያሉትን ፓሊሲዎች በጥራት ማውረድና መፈጸም ላይ ያሉ ችግሮችና የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ነውም ብለዋል።
    በባለሀብቱ በኩል ያለው የማስፈጸም አቅም ማነስ ችግር ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያመርት አድርጎታል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አንድ ባለሀብት ብዙ ገንዘብ አፍስሶ የገነባውን ፋብሪካ በተማረና አቅም ባለው ሠው እንዲመራው ከማድረግ ይልቅ የትምህርት ደረጃው ብቁ ያልሆነን ዘመዱን በማስቀመጥ ወደኪሳራና ብክነት ይገባሉ ይሄ መስተካከል አለበት ሲሉም ነው የገለጹት።
    መንግሥት ይሄንን ችግርንለመፍታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአቅም መገንባት ሥራን እንድሚያከናውንም አስታውቀዋል።
    በባለሀብቶች በኩልም የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ባቀረቡት ማብራሪያ፤ “ባለሀብቱ ጋርም ችግሮች አሉ፤ ያልተገባ ውድድር የአመራር አቅም ማነስ እና መሰል ችግሮች መፈታት ያሉባቸው ማነቆዎች ናቸው” ብለዋል።
    መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪው በሰጠው ትኩረት በዘርፉ ለውጦች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ ጀማል፤ ሚድሮክ ላይ በተደረገ ሪፎርምና አገራዊ ድጋፎች ከአምናው ገቢያችን እጥፍ ገቢ አግኝተናል ሲሉም አስታውቀዋል።
    ኢትዮጵያ ታምርት የሚለው ንቅናቄ በደንብ ከተተገበረ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላልም ነው ያሉት።
    መንግሥትም ህዝቡም መወቀስ ካለበት በአገር ውስጥ ምርት መጠቀም ላይ ያለባቸው ከፍተኛ ውስንነት መሆኑን አንስተው፤ እንደ አገር የኢትዮጵያን ምርት የመጠቀም ንቅናቄ መፍጠርና መተግበር ከተቻለ ከፍተኛ እመርታ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
    የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በድሬደዋ ከተማ ያዘጋጀውና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያተኮረው የፓናል ውይይት ተጠናቋል፤ ድርጅቱ ይሄንን ሃላፊነት በራሱ ተነሳሽነት ወስዶ በስኬት በማጠናቀቁ ሚኒስትሮቹና የእለቱ እንግዶች አመስግነዋል።