ዛሬ በአሰተዳደራችን ድሬዳዋ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተዘጋጀውና “ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘው የፓናል ውይይት ላይ ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴና የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በማሰመልከት ለፓናል ውይይቱ ተዳሚዎች ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ክቡር ከንቲባዉ ባቀረቡት ጽሁፋቸው በአሰተዳደራችን ለአገራችን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ ከሆነዉ ኮተን ፋብሪካ አንስቶ አስከ አሁን ባለዉ የኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን በ ድሬዳዋ አሰተማማኝ ሰላም በማሰፈን ኢንቬስተሮች ያለ ምንም የጸጥታ ስጋት ለወደብ ቅርብ በሆነችዉ ከተማችን ድሬዳዋ ኢንቬስት ማድረግን ቀዳሚ ምርጫቸዉ እንዲያደርጉ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር አክለዉም የኢንዱስትሪው ዘርፍ እምቅ ሀብቶች ባላት ከተማችን ድሬዳዋ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነም ጨምረዉ ገልጸዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለዉጥ ማምጣት የሚቻለዉ በዋናነት በግል ባለሀብቱ የነቃ ተሳትፎ ነው ያሉት ክቡር ከንቲባው በአስተዳደሩ በኩልም መሠረተ ልማትን ማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ችግር ማቃለል ስለሚጠበቅ በዚያ አግባብ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በድሬዳዋ ከተማ ያዘጋጀውና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያተኮረው የፓናል ውይይት ተጠናቋል፤ ድርጅቱ ይሄንን ሃላፊነት በራሱ ተነሳሽነት ወስዶ በስኬት በማጠናቀቁ ሚኒስትሮቹና የእለቱ እንግዶችን አመስግነዋል።


