የገጠሩ ማህበረሰብ የውሃ ሃይጅን እና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

    በድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ የተመራ ከቢሮ ማናጅመንት አባላት እና ከተለየዩ ሴክተር ተቋማት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ትኩረቱን በውሃ፣ ሃይጅን እና ሳኒቴሽን አገልግሎት አጠቃቀም ላይ ያደረገና አምስት የገጠር ቀበሌዎችን የሸፈነ የመስክ ምልከታ ተካሄዷል፡፡
    በጉብኝቱ ወቅት የመጸዳጃ ቤት ሽፋናቸውን መቶ ፐርሰንት በማድረስ ሜዳ ላይ ከመጸዳዳት ነጻ መሆናቸው ከአስተዳደሩ እና ከጤና ቢሮ ማናጅመንት በተውጣጣ አረጋጋጭ ኮሚቴ ተረጋግጦ በየቀበሌዎቻቸው የሚዘጋጀውን የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም እየተጠባበቁ ያሉትን የአሰሊሶ እና በለገኦዳ ጉዱንፈታ ቀበሌዎች የተከናወኑ ተግባራትን፣ እንዲሁም በመልካጀብዱ እና በለገኦዳ ጉዱንፈታ ጤና ጣቢያ በበጀት ዓመቱ በዋን ዋሽ ፕሮግራም እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን፣ በዋሂል ጤና ጣቢያ የተቋቋመውን ገበያን መሰረት ያደረገ የሳቴሽን ማዕከል እና በጤና ጣቢያው የሚሰጠውን አገልግሎት ለመመልከት ተችሏል፡፡
    የውሃ፣ ሃይጅን እና ሳኒቴሽን አገልግሎትን በማህበረሰብ እና ተቋማት ደረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ከ60-80 በመቶ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን እንዲሁም የገጠሩ ማህበረሰብ የውሃ ሃይጅን እና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን የተናገሩት የጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በጤና ቢሮና በኢትዮ-ጣሊያን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ትብብር የሽንት ቤት ክዳን እና ተዛማጅ ምርቶችን የማምረት ስልጠና ወስደው የዕውቅና ሰርተፍኬት የተሰጣቸው ወጣቶች በተሰጣቸው ስልጠናና የሥራ ማስጀመሪያ ካፒታል ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙ የመፀዳጃ ቤት ግብአቶችንና ሌሎችንም ተያዥ ምርቶችን በማምረት በተመጣጣኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረባቸው የህብረተሰቡን የጉዞ ወጪ ከመቀነሱ ባሻገር ለወጣቶቹም የገቢ ምንጭ እንዲሁም ለገጠር ቀበሌዎቹ ንፅህና አጠባበቅ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡
    የኢትዮ-ጣሊያን ቴክኒክና ሞያ የትምህርትና ስልጠና ምክትል ዲን አቶ ኤልያስ አህመድ በበኩላቸው በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግ እና ዘላቂ የሆነ የውሃ፣ ሃይጅን እና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ማህበረሰቡ እራሱን ከተላላፊ በሽታዎች በመከላከል ጤናማ እና አምራች ዜጋ እንዲሆን የሚደረገውን ጥረት በቀተቀናጀ እና ትብብር መንፈስ ሊደግፍ እንደሚገባና ለመፃዳጃ ቤት ሚያስፈልጉ የኮንስትራክሽን ምርቶችን ለማምርት ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ የገቡ ወጣቶች ማህረሰቡን በሞያዊ ስነ-ምግባር እና እራሳቸውንም መቀየር በሚችሉበት መንገድ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ ተናግረዋል ሲል የዘገበዉ የጤና ቢሮ ኮሙኒኬሽን ክፍል ነዉ