2ኛ ዙር የዳሽን ከፍታ የስራ ፈጠራ ስልጠናና ውድድር ፕሮግራም ተጠናቀቀ ፡፡
ዳሸን ባንክ ሁለተኛውን ዙር የዳሸን ከፍታ የስራ ፈጠራ ስልጠናና ውድድር መርሀ-ግብር በድሬዳዋ አስተዳደር ላለፍት አምስት ቀናት ያካሄደ ሲሆን መርሀ-ግብሩም ባለፈዉ ዓመት በስራ ፈጠራ ላይ ያተከረ ስልጠናና ዉድድር በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ላይ ተከናዉኖ በርካታ ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ሲሆን ወድድሩና ስልጠናዉም በድሬዳዋ ፣ አዳማ ፣ መቀሌ ፣ ባህር ዳር ፣ ሃዋሳ እንዲሁም በአዲስ አበባ ላይ ተከናዉኗል፡፡
በያዝነው ዓመትም መርሀ-ግብሩ በስድስት ከተሞች ማለትም በሃዋሳ፣ በድሬዳዋ ፣ በአዳማ ፣ በደሴ ፣ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ላይ እንዲከናወን ታቅዶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል ፡፡ በድሬዳዋ አስተዳደር ያለፍትን አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዳሸን ባንክ ሁለተኛው ዙር የዳሸን ከፍታ የስራ ፈጠራ ስልጠና ውድድር ማጠቃለያ መርሀ-ግብር በዛሬው እለት የተካሄደ ሲሆን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባን በመወከል በእለቱ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ብሩክ ፈለቀ በተለይም ሀገሪቱ በስራ ፈጠራ ዘርፍ የጀመረችውን ጥረት ለማገዝ ዳሽን ባንክ እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበው ሰልጣኞችም ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩም አሳስበዋል ፡፡
በዚሁም መርሀ-ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የዳሽን ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ ኑሪት መሀመድ በበኩላቸዉ ዳሽን ባንክ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣትና ስራ አጥነትን ለመቀነስ ፕሮግራም ቀርፆ እየሰራ እንደሆነና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ቺፍ ፋይናንስ ኦፊሰር የሆኑት አቶ አለምነህ አበበ በበኩላቸው መርሀ-ግብሩ ዜጎች ስራ ፈጥረው ራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት እንደሆነ ጠቅሰው ባንኩም ለውድድሩ አሸናፊዎች ሽልማት እንዳዘጋጀና የስራ ሀሳብ ያላቸውንም እንደሚደግፍ ተናግረዋል ፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የወሰዱት ስልጠና በስራቸው ላይ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረዳቸው ተናግረው ባንኩ በቀጣይም የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል ፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይም ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል ፡፡


