የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ለውጥ እያመጣ ነው የድሬዳዋ ነዋሪዎች

    የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም በድሬዳዋ የተጀመረው የቅዳሜና የእሁድ ገበያ ሸማቾችና አምራቾችን የሚያገናኝና ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
    የግብርና ቢሮ በበኩሉ ባለፉት የገበያ ቀናት አበረታች ውጤት በግብርና ምርቶች ላይ እየተገኘ በመሆኑ ገበያው አመቺ በሆኑ በየአካባቢዎች ይስፋፋል ተብሏል፡፡
    በድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ቢሮ የህብረት ስራ ማህበራት ግብአትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን አብዱረህማን በህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በከተማ እና በገጠር እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ካለፉት ጊዜያት ጀምሮ የሚስተዋለውን ወቅታዊ የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ያግዝ ዘንድ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከ38ቱም ገጠር ቀበሌዎች የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዎጋ ለማህበረሰቡ እያቀረቡ እንደሆነ አቶ አቶ ኑረዲን አብራርተዋል፡፡
    ሸማቾች፣ ነጋዴዎችና አምራቾች የሚያገናኝ የቅዳሜና የእሁድ ገበያ በስራ ላይ የሚውል ሲሆን ቲማቲም ሽንኩርት ድንች መሰል የግብርና ምርቶች መቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡
    እንደ አቶ ኑረዲን ገለፃ ባሳለፍነው ሳምንት የአንድ ኪሎ የሽንኩት ዋጋ መደበኛ ገበያ ላይ 50 ብር ሲሸጥ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ላይ ሰላሳ ሰባት ብር እንዲሸጥ አድርገናል፣ ድንች አንድ ኪሎ 35 ብር መደበኛ ገበያ ላይ ሲሸጥ እኛ በሀያ ስምንት ብር ሸጠናል እንዲሁም መሰል የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰባችን አቅርበናል ብለዋል፡፡
    የገጠሩ ማህበረሰብም መጠቀም አለበት በሚል የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ገጠር ወስደን እንሸጥ አድርገናል ስኳር፣ ኦሞ፣ ዘይት፣ እንዲሁም የፅዳት እቃዎችን ጭምር ለገጠሩ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል፡፡
    አርሶ አደሩ ባመረተው ምርት ሳይጠቀም ደላሎች እየተጠቀሙ ነው ይህን የደላሎችን ተግባር ለማስቀረት የግብርና ቢሮ የህብረት ስራ ማህበራት ግብአትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ሰፊ ስራ መሰራቱን አቶ ኑረዲን አብራርተዋል፡፡
    ባለሞያዎቻችን ገጠር ድረስ በመሄድ ቀንና ማታ በማሰራት የደላሎችን ስራ የማክሸፍ እና የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ለአርሶ አደሩ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
    በከዚራ የቅዳሜ እና የእሁድ በገበያው ስፍራ ሲገበያዩ የነበሩት አቶ ሰለሞን እንግዳ እንደተናገሩት፤ የግብርና ምርቶች በበቂና በታላቅ ቅናሽ ቀርበዋል፡፡
    አንድ ኪሎ የሽንኩት 37 ብር፣ ድንች አንድ ኪሎ 28 መሸመታቸውን ገልፀዋል፡፡
    ወ/ሮ ሰአዳ አሊ ይህ የቅዳሜና የእሁድ ገበያ መጀመሩ በየጊዜው እየጨመረ የሚገኘውን የሸቀጦች ዋጋና የኑሮ ውድነት ለመቋቋም አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
    የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች አስፈላጊና ለኑሮ ውድነቱን መቀነስ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ያሉት ደግሞ አቶ ጥበቡ ሀይሌ ናቸው፡፡
    አስተዳደሩ መቆጣጠር ያለበት የግብርና ምርቶችን ዋጋ ለማስወደድ ከሸማቾች ጋር ተጋፍተው እየገዙ የሚገኙት ደላሎች እንደሆኑ አሳስበዋል፡፡ ነጋዴው አቶ ኡስማን አሊ በበኩላቸው የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች በአራቱም ማዕዘናት መስፋፋት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የምናቀርባቸው ምርቶች ተገቢውን ገበያ እያገኙ በመሆኑ ተደስተናል ብለዋል፡፡
    በየደረጃው የሚገኘው የንግድ ማህበረሰብ ነዋሪውን በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል እንደ አገር የተከሰተን ችግር ለመሻገር መረባረብ እንዳለባቸውም በግብርና ቢሮ የህብረት ስራ ማህበራት ግብአትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን አብዱረህማን ጥሪ አቅርበዋል፡፡