ከዚህ ቀደም ” የፈተናዎች መብዛት ከብልፅግና ጉዟችን አያስቆመንም ” በሚል መሪ ሀሳብ በድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት የብልፅግና ፓርቲ ድህረ-ጉባኤ የህዝብ ውይይት በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ የከተማና የገጠር ቀበሌዎች ላይ መካሄዳቸው ይታወሳል ። በዚሁም ጉባኤ ላይ የከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮን ጨምሮ በስሩ ያሉ ተቋማት በቀጣይ መስራት ያለባቸውን ስራዎች አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎች ከህብረተሰቡ ተነስተው የነበር ሲሆን እነዚህንም ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ቢሮው የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት የተለያዩ ስራዎችን በመሰራት ላይም ይገኛል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ በስሩ የከተማ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ፣ የደንብ ማስከበር ፣ የፅዳትና ውበት ፣ የቄራ እንዲሁም የመንገዶች ባለስልጣን ያሉ ሲሆን በነዚህም ተቋማት ላይ ከዚህ ቀደም ነዋሪው ህብረተሰብ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጂነር ኡመር ዱአሌ ተናግረዋል ።
በተለይም ከፅዳት ውበትና አረንጓዴ ልማት ስራዎች ጋር ተያይዞ በክቡር ከንቲባው መሪነት መላው የአስተዳደሩ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት ሳምንታዊ የፅዳት ዘመቻ በከተማዋ ላይ ይካሄድ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የፅዳት ዘመቻው በሁለት ሳምንት አንዴ እየተካሄደ ይገኛል ። የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በከተማዋ ላይ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያም በከተማም ሆነ በገጠር መጠነ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ኢንጂነር ኡመር ዱአሌ ተናግረዋል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር ሰፋፊ የሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ ከመሆኑም በዘለለ ስራዎቹም በተያዘላቸው ጊዜ ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲሰሩ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ኢንጂነር ኡመር ዱአሌ ተናግረው መጪው ወቅትም የክረምት ወራት እንደመሆኑ መጠን በከተማዋ ላይ የጎርፍ ችግር እንዳያጋጥም የተዘጉ ዲሾችን የማስከፈትና የማፅዳት ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል ።
ከዚህ ቀደም በከተማዋ ላይ ይስተዋሉ የነበሩትን ህገ-ወጥ ንግዶችና ህገ-ወጥ እርዶች እንዲሁም ሌሎች በህገ-ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስራዎችን ህጋዊ እንዲሆኑ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የደንብ ማስከበር ስራዎች መሰራታቸውን ኢንጂነር ኡመር ዱአሌ ተናግረዋል ። ይህ በእንዲህ እንዳለም በከተማዋ ላይ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሀ ፍላጎትን ለማሟላት ይቻል ዘንድም በጀት ተመድቦ የውሀ ጉድጓድ ቁፋሮ በመደረግ ላይ እንደሚገኝና ከዚህ ቀደምም የተጠናቀቁትን የውሀ ጉድጓዶችን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ አሁን ላይ የሚስተዋለውን የውሀ መቆራረጥ ችግር እንዲፈቱ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል ።
በአስተዳደሩ ከ 200 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት የተገነባው ቄራ በአካባቢው ላይ ካለው የውሀ ችግር ጋር ተያይዞ በታለመለት ጊዜ ወደ ስራ እንዳልገባና አሁን ላይ ግን ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝና በቀጣይ ቄራው ወደ ስራ በሚገባበት ወቅት ከድሬዳዋ አልፎ ለሌሎች አጎራባች አካባቢዎችም በእጅጉ ሊጠቅም እንደሚችል ተገልፆል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ብሎም በከተማ ስራ-አስኪያጅ ስር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ የነዋሪው ህብረተሰብ አስተዋፆ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለከተማችን እድገትና ብልፅግና ነዋሪው ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩላቸውን የበኩላቸውን አስተዋፆ መወጣት እንዳለባቸውም ነው የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጂነር ኡመር ዱአሌ የተናገሩት ።


