በድሬዳዋ አስተዳደር አዲሱን ነዳጅ ድጎማና ዋጋ ማስተካከያ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተገልፃል፡፡
የሀገራችን የነዳጅ አቅርቦት ከጎሮቤት ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ በመሆኑ ዋጋ ለማከፋፈል በተደረገው ጥረት ባለፉት አመታት መንግስት ከፍተኛ የእዳ ጫና የተመዘገበበት በመሆኑ ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ 81.2 ቢሊዮን ብር ኪሳራ መድረሱን ተገልፃል፡፡
ችግሩን ከወዲሁ ለመቅረፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የነዳጅ ሪፎርም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት የጸደቀ ሲሆን ይህንን የነዳጅ ማስተካከያ ተግባራዊ ለማደርግ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ እንዲሆን ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተገልፃል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር እንደገለጹት ከነዳጅ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በከተማችን በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት መኖሩን ገልጸው የሚመደበው ኮታ በተመለከተ የማሻሸያ ሀሳብ ቢቀርብም ምንም ምላሽ እንዳልተሰጠና በቀጣይ በሚደረገው የነዳጅ ድጎማና ዋጋ ማሻሻያ ተመን በተመለከተ የኮታ ምደባ መስተካከል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ከፊታችን ሐምሌ ጀምሮ የነዳጅ ድጎማ የዋጋ ተመን ማስተካከያ ተግባራዊ ለማድረግ ክልሎች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ አመራሩ ቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን መረጃና የዋጋ ተመን ማስተካከያ በተመለከተ የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ መፈጠር እንዳለባቸው ተገልፅዋል፡፡
ከነዳጅ መሸጫ ዋጋ ጋር ተያይዞ ወቅቱን የጠበቀ የዋጋ ክለሳ አለመደረጉ፣ ኮትሮባንድ ጥቁር ገበያ መስፋፋት እንዲሁም ከፍተኛ የእዳ ጫና በመከሰቱ ባለፉት ሶስት አመታት መንግስት 132.3 ቢሊየን ብር ኪሳራ መድረሱን የተገለጸ ሲሆን ሀገሪቷ ከነዳጅ ምርት ከ60-70 ቢሊዮን ብር መንግስት እየደጎመ እንደሚገኝ ተገልፃል፡፡
በነዳጅ ግብይት ሰንሰለት የሚታዩ ችግሮች፣ ከነዳጅ ዋጋ ኮታና ከታሪፍ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የነዳጅ ግብይት መሰረተ ልማት ውስንነት ፣የአሰራር ፣የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች አፈፃፀም ክፍተቶች በስፋት የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን የተገለፀ ሲሆን የቤንዚን አቅርቦት በተመለከተ 2.5 ወደ 2.9 ሚሊየን ሊትር እንዲያድግ ቢደረግም አሁንም የነዳጅ እጥረት እየተከሰተ መሆኑ ተጠቁሟል ፡፡
ለሚኒስትር ምክት ቤት ቀርቦ የጸደቀው የነዳጅ የዋጋ ተመን ማስተካከያ ሰነድ ተግባራዊ እንዲደረግ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች፣ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ በድጎማው የሚካተቱ ሲሆኑ የመንግስትና የግል ተሸከርካሪዎች በድጎማው እንደማይካተቱ ተገልፃል፡፡
በአዲሱ የነዳጅ ድጎማና የዋጋ ተመን ተግባራዊ ለማድረግ በከተማችን ውስጥ የሚገኙ ከ 5 ሺህ በላይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች መመዝገባቸውን ንግድ ፅ/ቤት አስተውቋል ፡፡
ምንጭ፡-የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ


