ባቡር በሀገራችን የትራንስፖርት ዘርፍ ትልቅ አስተዋፆ እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን በተለይም መንግስት ለዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት አዳዲስና እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ባቡሮችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለነዋሪው ህብረተሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ከመደረጉም በዘለለ የባቡር ጣቢያዎችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማስገንባት ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ተደርገዋል ።
ባቡር ለነዋሪው ህብረተሰብ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ ቢገኝም ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በባቡር ላይ ከፍተኛ የሆነ ስርቆት እየተስተዋለ ይገኛል ። ስርቆቶቹ በዋናነትም የባቡር ሀዲድ ብሎኖችን መፍታት ፣ የባቡር ድልድዮች ላይ ያሉ ብረቶችን እየቆረጡ መውሰድ እንዲሁም ከባቡር ጋር ተያይዞ ያሉ ሌሎች ማቴሪያሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያዎች በስፋት ይስተዋላሉ ።
እነዚህን ዝርፊያና ስርቆቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድም በዛሬው እለት በድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሀርቢ ቡህ ሰብሳቢነት ውይይት የተካሄደ ሲሆን በተለይም በባቡር ላይ የሚስተዋለውን ዝርፊያና ስርቆትን ለመከላከል የቅንጅት ስራዎችን መስራት እንደሚገባና በይበልጥም ግን ነዋሪው ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን በመሆን ችግሩን ለመፍታት መስራት እንደሚገባም ተገልፆል ።


