በድሬዳዋ አስተዳደር የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የእድገት ደረጃ ሽግግር እውቅና መርሀ-ግብር ተካሄደ

    በድሬዳዋ አስተዳደርና በፌደራል ትብብር በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች የከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከልነትና በቀዳሚነት የሚያረጋግጡ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ሲሆን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ከተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች መካከልም በከተማዋ የተገነቡት የኢንዱስትሪ መንደርና የኢንዱስትሪ ፓርክ ናቸው ፡፡
    እነዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ
    አነስተኛ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የድሬዳዋን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት የሚያረጋግጡ ብቻ ሣይሆኑ አልሚዎችና ነዋሪዎቿ ብሩህ ተስፋ የሚያሰንቁ ብሎም ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገትም የላቀ አስተዋፆ የሚያበረክቱም ናቸው ፡፡ በዛሬው እለትም በከንቲባ መሰብሰቢያ አዳራሽ በከተማው ላይ በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የእድገት ደረጃ ሽግግር ላመጡ የእውቅና መስጠት መርሀ-ግብርም ተካሂዷል ።
    በዚሁም መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሀርቢ ቡህ በተለይም የኢንደስትሪው ዘርፍ በየጊዜው እየተሻሻለ የመጣውን የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ብሎም የከተማዋ የኢንደስትሪ ልማት ስትራቴጂን ተከትሎ አንድ የኢንደስትሪ ዞን ቦረን ደጀን በማዘጋጀትና መሰረተ ልማቶች እንዲሟለ በማድረግ በርካታ ባለሃብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል ።
    አቶ ሀርቢ ቡህ አክለውም የተሰጣቸውን መሬትም ከታለመለት ዓላማ ውጭ የማዋል ችግሮች ቢታዩም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የጨርቃ ጨርቅ ፣ የቅባት ፣ የሳሙናና ዲተረጀንት ፤ የኮንስተራክሽን ግብአት አቅራቢ ኢንደስትሪዎች ወደ ተጨባጭ የማምረት ተግባር መሸጋገራቸውንም ነው አቶ ሀርቢ ቡህ የተናገሩት፡፡
    ነዋሪው ህብረተሰብ ብሎም ባለድርሻ አካላቶች በጋራ በመረባረብ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ የተሸጋገሩትን አካላቶች በቁጠባም ሆነ በሌሎች የመሰረተ ልማት ድጋፎች ከጎናቸው መቆም እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ምክትል ቢሮ ሀላፊና የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኤጀንሲ ሀላፊ የሆኑት አቶ አብዲ ሙክታር ተናግረዋል ።
    በመርሀ-ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይም በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መስክ የእድገትና ደረጃ ሽግግር ላስመዘገቡ አካላት የእውቅና ሰርተፍኬት ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ ተቀብለዋል ።