በድሬዳዋ አስተዳደር በጤናው መስክ የሚነሱትን ጥያቄዎች ለመፍታት ዘርፈ-ብዙ ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ ።

    በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር በጤናው መስክ መሰራት ያሉባቸውን ስራዎች አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው የነበረ ሲሆን እነዚህም ጥያቄዎች በዋናነት የህብረተሰብ ጤና መድህን ተደራሽነት ላይ ያሉ ችግሮች ፣ የመድሀኒትና የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት ችግር ፣ የቢዮ አዋሌ ጤና ጣቢያ ላይ የሚገኘው የድንገተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ያለ ችግር ፣ በጤናው ዘርፍ የሰተሰማሩ ሞያተኞች የሙያ ስነ-ምግባርና ቸልተኝነት ፣ በጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ላይ ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት ፣ አዲሱ ሁለገብ ትምህርት ቤት ላይና ቃልቻ ቀበሌ ላይ እየተገነባ ያለው የጤና ተቋም ላይ ያለ ችግር ፣ በድልጮራ ሆስፒታል ላይ ያለው የማዋለጃ ክፍል የመፀዳጃ ቤቶች ችግር ፣ የላብራቶሪ ምርመራ የአገልግሎት መቆራረጥ ችግር እንዲሁም በሆስፒታሉ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የህክምና ባለሞያዎችን አስመልክቶ በዋናነት የተነሱ ችግሮች ነበሩ ።
    በድሬዳዋ ላይ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ የጤና ተቋማት ላይ የሚጠቀሙ አካላትን በመሰብሰብና ውይይት በማካሄድ በጤናው መስክ ሌሎች ያሉትን ችግሮች ማወቅ እንደተቻለና እነዚህንም ጥያቄዎች ለመፍታት እቅድ በማዘጋጀት ሰፊ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረው የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ወይም ሪፎርም እቅድ ከማዘጋጀት ባለፈ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር በቢሮም ሆነ በጤና ተቋማት ደረጃ ሰፊ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ።
    ከዚህ ቀደም በጤና ተቋማት ላይ ያልነበሩ የህክምና መሳሪያዎች ግዢ እንዲፈፀም የተደረገ ሲሆን በድልጮራ ሆስፒታል የተበላሹ የላብራቶሪ ማሽኖች ተጠግነው ወደ ስራ እንዲገቡም ከመደረጉ ባለፈ ሁለት ኤክስሬይ ማሽን በሆስፒታሉ ላይ እንዲገጠም የተደረገ ሲሆን የቢዮ አዋሌ ጤና ጣቢያ የድንገተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለመጀመርም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተው እንደተጠናቀቁና ለጤና ጣቢያ የሚያገለግል የህክምና ማሽን መገዛቱንም ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ።
    በስራዎች ላይና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር የሚፈጥሩ የጤና ባለሞያዎች ላይ የማስተካከያ ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝና በድልጮራ ሆስፒታል ላይ ከዚህ ቀደም ቅዳሜና እሁድ አገልግሎት አይሰጥባቸውም ሲባል የነበረው የላብራቶሪ ስራዎች አሁን ላይ ግን እንዲሰሩ መደረጉን ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረው በድልጮራ ሆስፒታል ላይ ያለው የማዋለጃ ክፍል የመፀዳጃ ቤቶች ችግርን ለመፍታትም ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ተገልፆል ።
    አዲሱ ሁለገብ ትምህርት ቤት ላይና ቃልቻ ቀበሌ ላይ እየተገነባ ያለው የጤና ተቋም ላይ ያለውን ችግር ለመፍታትም ዘርፈ-ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝና በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ ገጠር በጤናው መስክ ውጤታማ የሆኑ ስራዎች ይሰሩ ዘንድም ነዋሪው ህብረተሰብ የበኩላቸውን አስተዋፆ ሊወጡ እንደሚገባም የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ጠይቀዋል ።