በተለያዩ ከተሞች ተደብቀው የተገኙት ቦቴዎች ዛሬ እስከ 10 ሰዓት ተኩል ላይ ነዳጁን ማራገፋቸውን ሪፖርት ካላደረጉ እርምጃ ይወስድባቸዋል
===============
ከጂቡቲ ተነስተው አዲስ አበባና የተለያዩ ዋና ከተሞች መድረስ የነበረባቸው 200 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ከአዲስ አበባ ውጪ በየሠፈሩ ተደብቀው መገኘታቸውን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰዓረላ አብዱላሂ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በተለይ አዲስ አበባና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ላይ ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት ተከስቷል።
ይህም በህገወጥ መንገድ የነዳጅ ቦቴዎቹ በየመንደሩ ተደብቀው የኢኮኖሚ አሻጥር በፈጠሩ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፋር፣ መተሃራ፣ በሞጆ፣ በአዳማና በተለያዩ ከተሞች ተደብቀው የተገኙት ቦቴዎች ዛሬ እስከ 10 ሰዓት ድረስ ነዳጁን በሚፈለገው ማደያ ማድረስ እንዳለባቸው ለባለቤቶቹ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም 10 ሰዓት ተኩል ላይ ነዳጁን ማራገፋቸውን ሪፖርት ካላደረጉ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመው ይህንን ቁጥጥር የሚመራ ግብረሃይል ተቋቁሟል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።


