በዚሁ በአገር አቀፍ ደረጃ በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው የ 2014 ዓ/ም አፈፃፀም ግምገማና የ2015 ዓ/ም ዕቅድ ዝግጅት የምክክር መድረክ የስጋት ዳሰሳ፤ የመረጃ ጥራት ዳሰሳ፤ የአባላትና የመዋጮ አሰባሰብ መረጃና በቀረቡ ሪፖርቶች እንዲሁም በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድን አዋጅን በተመለከተ ያለበትን ደረጃ እና በአዋጁ የተካከተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ተብራርዋል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጲያ ጤና መድን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ በ 2014 ዓ/ም የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በ 894 ወረዳዎቸ ላይ መተግበር መቻሉንና የተጠቃሚዎች ቁጥርም ከ 45 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በበኩላቸው ከተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች የመጡትን ታዳሚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ በአስተዳደራችን የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድን ፕሮግራም ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ማህበረሰባችንን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግና ፕሮግራሙ እንደ ሃገር የተያዘለትን ግብ ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ በመቆየታቸው በ 2014 ዓ/ም የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድን አገልግሎት አፈፃፀምን የተሻለ ለማድረግ በተደረገ ርብርብ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
አቶ ዩሱፍ አያይዘውም ማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድን ህክምና አገልግሎትን ለማሻሻል የጤና ተቋማቶቻችንን በሚገባ በማዘጋጀት በኩል የተሠሩ ሥራዎች በጥሩ ደረጀ ላይ ያሉ ቢሆንም እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከአስተዳደሩ አመራሮች ጀምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በአፈፃፀም ግምገማና በምክክር መድረኩ ተገኝተው የማጠቃለያ ውይይቱን በመምራት ንግግር ያደረጉት በጤና ሚ/ር ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በ 2014 ዓ/ም በማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ውጤታማነት የድርሻቸውን ሚና የተወጡ አካላትን አመስግነው ከ 2014 ዓ/ም አፈፃፀም በተሻለ በ 2015 ዓ/ም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድን አባላትን ለማፍራት 75 % ለማድረስና የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዶክተር ደረጀ የጤና መድን አገልግሎትንና ሌሎች ፕሮግራሞችን አቀናጅቶ ለመሥራት የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ መሆኑን በመጠቆም ለጤና መድን አገልግሎት የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረው ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ከክልል እና ከሁለቱ ከተሞች ጤና ቢሮዎች ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ጤና ሚ/ር በግምገማና በምክክር መድረኩ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት አቅም በፈቀደ መጠን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል፡፡
የግምገማና የምክክር ተሳታፊዎች በኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ቅጥር ጊቢ ችግኞችን የተከሉ ሲሆን ድርጅቱንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል ሲል የዘገበዉ ድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኮሙኒኬሽን ነዉ


