ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር ፕሮግራም መንግስታዊ ያልሆነ አለም አቀፋዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን በሀገራችን ኢትዮጲያ ወላጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ ህፃናትን አሰባስቦ ከለላ በመስጠት ራሳቸውን ችለው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚያደርግና የቤተሰብ ማጠናከሪያ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ለቤተሰብና ለማህበረሰብ ተቋማት ድጋፍ በመስጠት ቤተሰብ እንዲጠናከርና ልጆች የመብቶቻቸው ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የሚሰራ ተቋም ነው ።
ኤስ ኦ ኤስ በድሬዳዋ አስተዳደር ከማርች 2022 ጀምሮ በጎዳና ተዳዳሪና አካል ጉዳተኛ ህፃናት ዙሪያ ፕሮጀክት ቀርፆ እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን ይህንን ፕሮጀክትም በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ ለመተግበር ይቻል ዘንድም በዛሬው እለት በኪሊዮፓትራ ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በይፋ የማስጀመርና የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል ።
መንግስት በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ በተለያዩ የማህበራዊ መስኮች እየሰሩ የሚገኙ የሲቪክ ማህበራትን ድጋፍ ከማድረግ ጋር ተያይዞ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ስልታዊ በሆነ አግባብ እንደሚሰራና ኤስ ኦ ኤስም በጎዳና ላይ ለሚገኙ ህፃናት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ተሰማ ተናግረው የድሬዳዋ አስተዳደር በቀጣይም ኤስ ኦ ኤስ በከተማው ላይ ለሚሰራቸው ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አቶ ግርማ ተናግረዋል ።
ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር በሀገራችን ኢትዮጲያ ከዛሬ 46 አመት በፊት ስራ እንደጀመረና በእነዚህ አመታት ውስጥም በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደር ውስጥ ትላልቅ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ በኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር በኢትዮጲያ የምስራቅ ኢትዮጲያ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አንዱአለም ጌታቸው ተናግረው አሁን ላይ በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ ኤስ ኦ ኤስ የጀመረው ፕሮጀክትም አካል ጉዳተኞች ላይ ለሚቀጥሉት ሶስት አመት እንዲሁም ወደ 2 ሺህ 700 የሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናትና ቤተሰብን ድጋፍ የሚሰጥው ፕሮጀክት ደግሞ ለሚቀጥሉ አምስት አመት ተግባራዊ እንደሚሆንም ነው አቶ አንዱአለም ጌታቸው የተናገሩት ።


