ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን በተለያዩ መርሀ ግብሮች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የድሬደዋ አስተዳደር ሴቶች ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ ህዳር 11 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን በዓለም ደረጃ ለ33ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ’’ ምቹ እና ሰላማዊ ኢትዮጵያ ለሁሉም ህጻናት!’’ በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች እንደሚከበር የድሬደዋ አስተዳደር ሴቶች ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ጫልቱ ሁሴን በዛሬው እለት ለሚዲያ አካላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ የሴቶች ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን ለመደገፍ በርካታ ስራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን የገለጹት ሀላፊዋ ወ/ሮ ጫልቱ በተለይም ለህጻናቱ ድጋፍ በማድረግ በኩል የአስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች 0.25% ከደሞዛቸው እየተቆረጠ ለህጻናቱ ገቢ እየተደረገ እና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፎችም በማስባበር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን ሲከበርም በዓሉ ከማክበር ባሻገር የህፃናትን ሀሳብ የሚደመጥበት፣የህፃናት ተሳትፎን ትርጉም ባለው መልኩ የሚረጋገጥበት፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በህፃናት ሁለንተናዊ እድገት ላይ የሚወያዩበት እና በህፃናት ላይ አጽንኦት ሰጥተው በጋራ ለመስራት ምቹ መደላደል በመፍጠር ለማክበር መዘጋጀቱን ገልጸዋል::

በዋናነት የህፃናት ቀን ሲከበር በመንከባከብ ያሉ የህፃናት ማሳደጊዎችን ድጋፍ በማድረግ፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ፣ የህፃናት መብት እና ደንህነት የሚረጋገጥበት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መድረኮች እንዲሁም ህፃናትን በሳተፈ መልኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የፓናል ወይይት በማካሄድ የሚከበር መሆኑን ሀላፊ ወ/ሮ ጫልቱ ገልጸዋል፡፡

በዓሉን አስመልክቶ ከሚከናወኑ መርሀ ግብሮችም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት አማራጭ ድጋፍ እንዲያገኙ የተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢ ፕሮግራሞች የሚከወኑ ሲሆን በማቆያ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲሁም በአደራ ቤተሰብ እንዲያድጉ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው ሀላፊዋ ያስረዱት፡፡ በመጨረሻም በቢሮ በዓሉን አስመልክቶ በሚዘጋጁት የተለያዩ መርሀ ግብሮች ላይ መላው የአስተዳደሩ ነዋሪም እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡