መልዕክት

    የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲህያ አደን መልዕክት

    ምክር ቤታችን በድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 መሰረት ከአስተዳደሩ ህዝብ የተወከለ እና ሉዓላዊ  ስልጣን  በውክልና የተሰጠው  ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ህገ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡

    ምክር ቤታችን ከተማና ገጠሩን የወከሉ 106 ወንድ 83 ሴት አባላት ያሉት ሲሆን ፤ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት በተሻሻለው የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 11/2009 መሠረት በየጊዜው ራሱን እየፈተሸ  የሀገሪቱን ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች  እንደ አስተዳደሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ተጨባጭ ሁኔታ እንዲፈፀሙ ማስቻል ፤ ለአስተዳደሩ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ህጎች ማውጣትና ተፈጻሚነታቸው መከታተልና መቆጣጠር ፤ በመንግስት አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት ፤ በመልካም አስተዳደር የነዋሪውን ተጠቃሚነት ማረጋጥ የመሳሉት ዋና ዋና  ተግባራቱ ናቸው፡፡

    ምክር ቤታችን ለ3ኛ ዙር በአዲስ መልክ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ዋነኛ የምክር ቤቱ አላማ የሆነውን የህዝብ ውክልናን ለመወጣት የሚስችሉ በሁሉም የአስተዳደሩ ቀበሌዎች ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር የአስተዳደሩ ምክር ቤት ተመራጮችና የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድሬዳዋ ተወካዮች ጋር በመሆን የህዝቡን የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር  እንዲሁም የልማት ጥያቄዎችን ለመስማት የሚያስችሉ ተከታታይነት ያላቸውን ከህዝብ ጋር የሚደረጉ የገጽ ለገጽ የህዝብ ውክልና መድረኮችን በተተናከረ መልኩ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በህዝብ ውክልና መድረኮች በነዋሪው ህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ወደ አስፈጻሚ አካላት በመውሰድ ምላሽ እንዲሰጡበት እና በተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ የአስተዳደሩን ህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የተተናከረ ምክር ቤታዊ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡  በተመሳሳይም በምከክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በኩል  በሚያካሂዳቸው የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች እና በሰጣቸው ግብረመልሶች የአስፈጻሚውን ውጤታማነት ለማጎልበት ከማስቻሉም በላይ የህዝብና የመንግስት ሀብትና ንብረት ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲዳብር የሚደረጉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በቀጣይ ይበልጥ በማጠናከር ውጤታማ ለማድረግ ከምንግዜውም በላይ እንድንረባረብ ከህዝብ የተጣለብንን አደራ ለተጠቃሚዎች ፣ ለባለድርሻ አካላት መረጃ ለመስጠትና ለተቋሙ እርካታ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ለማስቻል ይህ ፖርታል መዘጋጀቱን ሳበስር በደስታ ነው ፡፡

    አመሰግናለሁ!!