በድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እና የቢሮው ተጠሪ ተቋም በሆነው የድሬዳዋ ሥራ አመራር እና ካይዘን ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሠራተኞች ከራስ ለራስ የተደረገ የበጎ ተግባር ውጤት::

    የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እና የቢሮው ተጠሪ ተቋም የሆነው የድሬዳዋ ሥራ አመራር እና ካይዘን ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሠራተኞች በ 01ቀበሌ ሲያስገነቡት የነበረውን የወ/ሮ አሁዶ ጅብሪል አጠናቀው በዛሬው እለት አስረክበዋል:: በአስተዳደር ደረጃ በየአመቱ በሚከናወነው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ሁሉም የአስተዳደሩ የመንግስት ተቋማት እዲሳተፉ አቅጣጫ መቀመጡን ተከትሎ በዘንድሮው ክረምት የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የአንድ አቅመ ደካማ ቤት ገንብቶ ለማስረከብ ኃላፊነት ወስዶ የነበረ ሲሆን የቢሮው እና የቢሮው ተጠሪ ተቋም የሆነው ድሬዳዋ ሥራ አመራርና ካይዘን ኢንስቲትዩት አመራሮች አና ሠራተኞችም በ01 ቀበሌ የሚገኘውን የወ/ሮ አሁዶ ጅብሪል ቤት አስገንብተው በዛሬው እለት የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ፣ የአስተዳደሩ የካቢኔ አባላት፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፊራኦል ቡልቻ፣ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደሩ የመንግስት እና የፓርቲ አመራሮች እና የ01ቀበሌ አመራሮች በተገኙበት አስረክበዋል። በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ እንደተናገሩት እንደ አስተዳደር የመንግስት ተቋማት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ የተቀመጠውን አቅጣጫ በመቀበል የቢሮው አመራሮች እና ሠራተኞች በዚህ የኑሮ ውድነቱ ፈተና በሆነባቸው ጊዜም ቢሆን ካላቸው ላይ ቀንሰው ይህን በጎ ተግባር ሰርተው ስላሳዩን ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። አቶ ሀርቢ አክለውም በቀጣይም እንዲህ አይነቱን በጎ ተግባር ሁሉም የመንግስት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እና ባለሀብቶች በግባር ቀደምነት በመሳተፍ በክረምት ብቻ ሳይሆን አመቱን ሙሉ ሊተገብሩት እንደሚገባም መልዕታቸውን አስተላልፈዋል።

    የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪሰ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይር ሀጂኑር በበኩላቸው ሳሎን እና መኝታክፍል ያለውን ቤት ለመገንባት አጠቃላይ ከ286,729 (ሁለት መቶ ሰማኒያ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሀያ ዘጠኝ) ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቅሰው ከዚህም ባለፈ ለቤቱ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብዓቶችንም ማሟላታቸውን ተናግረዋል:: አቶ ሀይር አክለውም የቤቱ የግንባታ ሂደት ሲያስተባብሩ ለነበሩ የኮሚቴ አባላት እንዲሁም መላው የቢሮው አመራሮች እና ሠራተኞች ላደረጉት ሁሉ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም እንደ ተቋም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አፈየሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል::