ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከባለሀበቶች፣ከፋይናስ ተቋማት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ፡፡

ድሬ ማይክሮ ፋይናስ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በአስተዳደሩ በከተማ እና በገጠር ለሚኖሩ የስራ ተነሳሽነት ያላቸውን ለሴቶች ለነጋዴዎች እና ለወጣቶች በብድር እና ቁጠባ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በመስጠት ዜጎች ራሳቸውን ቤተሰባቸውን እና አካባቢን መለወጥ ወደሚቻልበት ደረጃ በማሻገር የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህንኑ የፋይናንስ አገልግሎት አሰራርን ለማሳደግ እና ለማዘመንም ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከባለሀበቶች፣ከፋይናስ ተቋማት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በዛሬው እለት በኒው ሌቭል ሆቴል ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይት መድረኩም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ እና የድሬ ማይክሮ ፋይናስ የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ተቋሙ የዜጎችን ማህበራዊ ህይወት ለማሻሻል እና በአስተዳደሩ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተረጋጋ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ማምጣት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የፋይናንስ ተቋምን ለመፍጠር የያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት በርካታ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ባንኩን በማሳደግ በኩል ለሚደረገው ጥረት የፋይናስ ተቋማት፣ባለሀብቶች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ አበበም በበኩላቸው ተቋሙ መሰረታዊ ለውጦችን ማምጣት የሚያስችላቸውን ውስጣዊ የአፈጻጸም አቅሞችን በማሳደግም በተያዘው አመት በስድስት ወሩ344 ሚሊዩን ብር ብድር በማበደር እንዲሁም 745 ሚሊዮን ብር በቁጠባ ከህብረተሰቡ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የድሬ ማይክሮ የፋይናንስ አቅምን በማሳደግ በኩል በአስተዳደሩ የሚገኙ ባለሀብቶች የፋይናስ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ሀላፊው ጠይቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *