የሀብት ብክነትን ለመቀነስ የመሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማት በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚገባቸው ተገለፀ::

#DGCመስከረም 22/2017

በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት በአስተዳደሩ የሚገነቡ የመሰረተ ልማት ስራዎች በተቀናጀና በተናበበ መልኩ እንዲሆን ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር የመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር ስርአት ደንብ ተዘጋጅቶ የአሰራር ስርአቱ መዘርጋቱን ጠቁመው፤ የአሰራር ስርአቱን ለመተግበር በዛሬው ዕለት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የመሰረተ ልማት ስራዎች ሲሰሩ ጥራት ባለውና ለታለመላቸው ጊዜ በአግባቡ ካለምንም ችግር እንዲያገለግሉ የመሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማት እርስ በእርስ በተናበበ መልኩ ስራዎቻቸውን መስራት ይገባቸዋል ሲሉ ኢንጂነር ጀማል ተናገረው፤ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ የመሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማት በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚገባቸውም ገልፀዋል፡፡

የመሰረተ ልማት ቅንጅት ጉድለት ካለ በርካታ የሀገሪቱ ሀብት፣ ጊዜና ጉልበት እንደሚባክን የጠቆሙት ኢንጂነር ጀማል እነዚህን ብክነቶች ለመቀነስ የጋራ ቅንጅታዊ የአሰራር ስርአት ተቋማዊ በሆነ መሰረት መሰራት አለበት ሲሉ አመላክተዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ ቤት የመሰረተ ልማትና የማዘጋጃ ገቢ ማስተባበሪያ ሀላፊ የሆኑት አቶ ኢብሳ አሜ በበኩላቸው በዛሬው መድረክ የመሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማት በ2017 ዓ.ም ምን ለመስራት አቀዱ የሚለውን እንዲሁም በእቅዳቸው መሰረት ስራዎችን ሲሰሩ በተናበበ መልኩና በጋራ እንዲሆን የየተቋማቱ እቅዶች ቀርበው ውይይት መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በቅንጅትና በጋራ መስራት የመስተዳደሩን ሀብት ከብክነትና ከኪሳራ እንደሚጠብቀው እንዲሁም ማህበረሰቡ ጋር የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዳይፈጠሩና ለከተማዋ ውበትና ገፅታ አስፈላጊ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን የገለፁት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ፡-አብይ ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *