የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቹ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ወዳጆቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተፈጽሟል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ፥በስርዓተቀብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አርቲስት ነጻነት ሕዝብን እና ሀገርን ያገለገለ ታላቅ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ እንደነበር ተናግረዋል።
በርካታ ሥራዎችን መሥራት በሚችልበት ዕድሜው መለየቱን ጠቅሰው፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለአድናቂዎቹ፣ ለሙያ ባልደረቦቹ እና ለመላው ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ በበኩላቸው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ ሥራውን በሙያዊ ብቃት እና በጥልቅ ዕውቀት ያከናውን እንደነበር ገልጸዋል።
አርቲስቱ ለሙያው ዲሲፕሊንና ለጥበብ ጥራት ትልቅ ትኩረት የሰጠ የጥበብ ሰው እንደነበርም አቶ ነብዩ አንስተዋል።
በነፃነት ወርቅነህ ሥራዎች ላይ ጥናት ተደርጎ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ እና እንደ መማሪያ እንዲያገለግል እንደሚደረግም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት።


