አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ
ዒድ አል ፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ትርጉም ያለው የቅዱሱ የረመዳን የፆም ወር ማሳረጊያ ታላቅ በዓል ነው፡፡
ዕለቱ ሕዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱና በታላቁ የረመዷን ወር ለሀገራችን ሰላምና ፀጋ፤ ለመላው ህዝባችን ፍቅርና አንድነት ወሩን ሙሉ በፆምና በዱአ አሳልፎ ከፈጣሪ እዝነትና በረከት የሚቀበልበት ልዩ ቀን ነው፡፡
የዒድ አል ፈጥር በዓል የመተሳሰብና የመጠያየቅ፤ የመረዳዳትና የአብሮነት በዓል ነው፡፡
በዓሉ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ሲያደርገው እንደነበረው በአንድነት ተሰባስቦ ያለው ለሌለው በማካፈል ማህበራዊ ትስስሩን ይበልጥ አጠንክሮ በአብሮነት የሚያከብረው በዓል ነው።
አንድነትና ኅብረት፤ መደጋገፍና መረዳዳት በእስልምና ልዩ ስፍራ እንደሚሰጠው የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን የበርካታ ዕሴቶች ባለቤት የሆንን ህዝቦች ብቻ ሳንሆን ልዩነቶቻችን የኅብር ማንነትን ውበት ያጎናፀፉን ድንቅ ህዝቦች ነን፡፡
በዚህም መላ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ በመደጋገፍና በመተባበር እንዲሁም በመቻቻልና ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የአባቶቻችንን ባሕል በማዳበር ለመጭው ትውልድ የአንድነት አሻራችንን በማሳረፍ ሊሆን ይገባል።
መላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተቀደሰው የረመዷን ወር የተገነባውን የሥነምግባር ከፍታ በማይቋረጥ የበጎ ተግባራት ላይ በማዋል በአስተዳደራችን ሁለንተናዊ ሠላም እንዲሠፍን፣ ፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲረጋገጥ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታበረክቱ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለው።
በመጨረሻም በዓሉን ስናከብር ለዘመናት የገነባነውን የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የመከባበር እና የመደጋገፍ እሴት በማጠናከር ሀገራዊ የለውጥ ጉዟችንን ከዳር ለማድረስ በየተሰማራንበት ዘርፍ ሀገራችንን በሐቀኝነት በማገልገል የድርሻችንን እየተወጣን በተለይም በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሀዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ስል አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በድጋሚ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የብልፅግና፣ የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ።
ዒድ ሙባረክ!


