“በከተማና በገጠር የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን አቀናጅተናል። እንዲሁም ነባር የጎብኚ መዳረሻዎችን አሻሽለናል። አዳዲስ መዳረሻዎችንም አልምተናል። እነዚህ ሁሉ በተለየትኩረት ከሠራንባቸው የለውጥ ማሳያዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ሀገራችን ከዚህ በፊት ከነበሯት የጎብኚ መዳረሻዎች ላይ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ብዙ ጨምረናል። መዳረሻዎቹም መላው ሀገራችንን ያካለሉ ናቸው። ከሀገራችን ስፋትና ከመብዛት አንጻር ያልደረስንባቸውና በዕቅድ ላይ ያሉ ብዙ መዳረሻዎችም በቀጣይ ይገነባሉ።

በእጃችን ላይ ያሉ የጎብኚ መዳረሻዎችን በሚገባ አገልግሎት ላይ ማዋልና ከዚህም ሊገኝ የሚችለውን ሀገራዊ ጥቅም ሁሉ መሰብሰብ ተገቢና በቀጣይ ለምንጓዘው አቅጣጫ ትልቅ ግብዓት የሚሆን ነው። ከዚህ አንጻርም ብዙዎችን በፍጥነት ወደ ሥራ አስገብተናል፤ ትሩፋቶችንም እያጣጣምን እንገኛለን።

በእነዚህ ጥረቶች ምክንያት ሀገራችንን የሚጎበኙ የውስጥም ይሁን የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር በጥሩ ሁኔታ እያደገ ነው። ይሁንና ዘርፉ ከፍተኛ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።

ሀገራችን ከቱሪዝም ሊገኝ የሚችለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ጥቅሞች ሁሉ ከቀረው ዓለም ጋር ተወዳድራ እንድታገኝ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ወደ ሀገራችን መሳብ አለብን። ለዚህም የተለያዩ ስልታዊ መለኪያዎች (Strategies) ነድፈን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።”

የመደመር አንቀፅ ገፅ 272-273

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *