***************
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትላንት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 688 ተማሪዎች ባስመረቀበት ደማቅ ስነ-ስርዓት ላይ፣ በኬምስትሪ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ዳዊት ከተማ የዕለቱ ደማቅ ኮከብ ሆኗል።
የድሬዳዋ ተወላጅ የሆነው ዳዊት በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከወሰዳቸው 57 የትምህርት አይነቶች መካከል 50 “A+” እንዲሁም ቀሪዎቹን 7 ትምህርቶች “A” በማምጣት በጠቅላላ 4 ነጥብ የላቀ ውጤት ተመራቂ መሆን ችሏል።
ዳዊት ለዚህ አስደናቂ ስኬት የበቃው ጊዜውን በእቅድና በአግባቡ በመጠቀም መሆኑን ለኢቲቪ የገለጸ ሲሆን፣ ምንም እንኳን ቤተሰቦቹ በአቅራቢያው ቢገኙም ሙሉ ትኩረቱን ትምህርቱ ላይ ለማድረግ ወደ ዩኒቨርሲቲ ግቢ በመግባት በንቃት ይከታተል እንደነበር ተናግሯል።
የኬምስትሪ ትምህርት ዘርፍ ወደ ተግባር ተኮር ስራ የሚቀየር በመሆኑ፣ በቀጣይ ችግር ፈቺ ምርምርና ጥናቶችን በማካሄድ ለሀገሩ የሚጠቅም ስራ ለመስራት መዘጋጀቱንና ወደ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ቢሸጋገርም ራሱን በማስተማር ለበለጠ ውጤት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።


